የሰብዓዊ መብት እና የአየር ንብረት ለውጥ ረቂቅ ድንጋጌ

የሰብዓዊ መብት እና የአየር ንብረት ለውጥ ረቂቅ ድንጋጌ

መግቢያ:

በተባበሩት መንግስታት ቻርተር፣ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ የአለማቀፍ የኢኮኖሚ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ስምምነት፣ የአለማቀፍ ሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት፣ በቬይና አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስብሰባ ድንጋጌና የተግባር መርሃግብር (ፕሮግራም)፣ በተባበሩት መንግስታት የቀደምት (ኢንድጅነስ) ህዝቦች ድንጋጌ፣ በናጎያ ፕሮቶኮል እና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን በያዙ ዓለማቀፍ ሠነዶች በመመራት፥

በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ አካባቢ (ኢንቫይሮመንት) ስብሰባ የስቶክሆልም ድንጋጌ፣ በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ መዋቅር (ፍሬምዎርክ) ስምምነት፣ በአለማቀፍ የብዝሃ ህይዎት ስምምነት፣ በአለማቀፍ የተፈጥሮ ቻርተር፣ በተባበሩት መንግስታት የባህር ህግ ስምምነት፣ በሪዮ የአካባቢ ጥበቃ እና የልማት ድንጋጌ፣ እንዲሁም በሌሎች ጠቃሚ  አለማቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ህግ ስምምነቶች በመመራት፥

ሁሉም የሰብዓዊ መብቶች አለማቀፋዊ፣ ተደጋጋፊ እና የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በድጋሜ በመቀበል፥

በመሬት ላይ የሚኖር ማንኛውም ህይዎት ከጤናማ የመሬት ስርዓት ጋር ያላቸውን ትስስር እና ተደጋጋፊነት  በመቀበል፥

በሰው ልጆች የኢንዱስትሪ እና የእለት ተዕለት የፍጆታ ተግባራት ምክኒያት የሚከሰት የአየር ንብረት መዛባት በድሆች፣ በሴቶች፣ በህጻናት፣ ተጋላጭ በሆኑ ትናንሽ ደሴት ማህበረሰቦች፣ ባላደጉ እና በማደግ ላይ ባሉ ሃገሮች፣በመጭው ትውልድ እና ብዛት ያላቸው ሰብዓዊ ባልሆኑ የተፈጥሮ ሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ያልተመጣጠነ ጉዳት በመቀበል፥

በፍርድ ቤቶች እና አለማቀፍ እውቅና ባላቸው የህግ ሙህራን የተረጋገጠው በሰብዓዊ መብቶች እና የተረጋጋ፣ ጤናማና የተማላ አካባቢ (ኢንቫይሮንመንት) መካከል ያለው ጥምረት ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሰብዓዊ መብቶችን የሚያጠቃልል መሆኑን በመቀበል፥

ሁሉም የሰው ልጆች እና ሰብዓዊ ያልሆኑ የተፈጥሮ ሰዎች በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የጉዳት ሰለባ መሆናቸውን በመቀበል፥እንዲሁም ሁሉም ሰዎች ሰብዓዊ ያልሆኑ የተፈጥሮ ሰዎችን መብት የማክበር እና የመጠበቅ የሞግዚትነት ሃላፊነት እንዳለባቸው በማመን፥

የአየር ንብረት ለውጥ በዛሬው እና በመጭው ትውልድ የእለት ተዕለት ኑሮ እና ደህንነት ላይ የሚያስከትለውን ስጋት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፥

በአየር ንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ዓሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር፣ ለአየር ንብረት መዛባት ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ርብርብ የገበያ ሁኔታ የበላይነትን ቦታ መያዙ እና በአለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ህጎች ውስጥ የንግድ ድርጅቶች (ኮርፖሬት አክተርስ) ለሚያደርሱት የሰብዓዊ  መብትና የአካባቢ ጥበቃ ህግ ጥሰት ቀጥተኛ ሀላፊነት አለመኖሩ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ሊያስከትል የሚችለው የከፋ ተጽዕኖ በጥልቀት ስላሳሰበን፥

የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል የሚችለውን በቀላሉ ሊቀለበስ የማይችል አሉታዊ ተጽዕኖ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ሃገራት እና ሌሎች ተቌማት ሊኖራቸው የሚገባውን ሃላፊነት እና ተጠያቂነት በአስቸኴይ መወሰን አስፈላጊ መሆኑን በማመን፥

የሚከተሉት መርሆዎች ተደንግገዋል:

ክፍል ፩

 1. የሰብዓዊ መብቶች እና የአየር ንብረት ፍትህን የማረጋገጥ ቍርጠኝነት ተደጋጋፊ እና የማይነጣጠሉ ናቸው::
 2. ማንኛውም ሰው የተረጋጋ፣ ጤናማና የተማላ ስነ-ምህዳር ባለው የመሬት ስርዓት የመኖር፥ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን የማንሰራራት፣ የማለማመድና ቅነሳ ሂደት ፍትሃዊ ተጠቃሚ የመሆን መብት አለው::
 3. ማንኛውም ሰው የመጭውን ትውልድ ተገቢ የሆነ ፍላጎት በማይጎዳ መልኩ የዛሬውን ትውልድ ፍትሃዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ምቹ የሆነ የአየር ንብረት የማግኘት መብት አለው::
 4. ማንኛውም ሰው ለጤናው እና ለኑሮው መሰረት የሆነውን የአካባቢ ለውጥ መከሰትን በተመለከተ መረጃ የማገኝት እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ የመሳተፍ መብት አለው::
 5. ማንኛውም ሰው ከአካባቢ ብክለት፣ መመናመን እና አካባቢን በካይ ከሆኑ ልቀቶች ነጻ የሆነ የተሻለ የጤና ደረጃ የማግኘት መብት አለው:: እንዲሁም የአለማቀፍ የሙቀት መጨመር ከሁለት ዲግሪ ሴንትግሬድ በታች የሆነበት እና ነጻ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አለው::

ክፍል ፪

 1. ማንኛውም ሰው በአየር ንብረት ለውጥ ምክኒያት ሊደርስ የሚችለውን የከፋ ጉዳት ለመከላከል እና ለመቀነስ ኢንቨስት የማድረግ፣ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ምክኒያት አደጋ ሲከሰት ጊዜውን የጠበቀ እርዳታ የማግኘት መብት አለው::
 2. ማንኛውም ሰው የአየር ንብረትን በተመለከተ መረጃ የማገኝት መብት አለው:: የሚሰጠው መረጃ ጊዜውን የጠበቀ፣ ግልጽ፣ በቀላሉ ሊገባ በሚችል እና ያልተገባ ገንዘብን በማይጠይቅ መልኩ መሆን አለበት::
 3. ማንኛውም ሰው የአየር ንብረትን በተመለከተ የመሰለውን አመለካከት በነጻነት የመያዝ፣ የመግለጽ፣ እንዲሁም ሃሳብን እና መረጃን በነጻነት የማሰራጨት መብት አለው::
 4. ማንኛውም ሰው የአየር ንብረት እና የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት የማግኘት መብት አለው:: ይህም ትምህርት ከተለያዩ አመለካከቶች የመማር መብትን፣ ሰብዓዊ ያልሆኑ የተፈትሮ ባህሪያትን ለመረዳት በሚያስችል እና የተሻለ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን ለማወቅ በሚያስችል መልኩ የመማር መብትን ያጠቃልላል::
 5. ማንኛውም ሰው በአየር ንብረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ በሚችሉ ዕቅድ የማውጣት እና ውሳኔ የማሳለፍ ተግባራትና ሂደቶች ላይ ነጻ፣ ንቊ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ የማድረግ መብት አለው::  ይህ መብት የታቀዱ ተግባራት በአየር ንብረት እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ ሊኖራቸው ስለሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቅድመ ምርመራ ማድረግን፣ በእኩልነት የመደመጥ መብትን፣ እና ከተጽዕኖ ነፃ የሆነ ተሳትፎ የማድረግ መብትን ያጠቃልላል::
 6. ማንኛውም ሰው የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ወይም በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰብዓዊም ይሁን ሰብዓዊ ያልሆኑ የተፈትሮ ሰዎችን መብት ለማስከበር በነጻነት እና በሰላማዊ መንገድ በማህበር የመደራጀት መብት አለው::
 7. ማንኛውም ሰው በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ለሚደርስበት ጉዳት ወይም የጉዳት ስጋት በአስተዳደራዊ ወይም በህግ የዳኝነት ስልጣን በተሰጣቸው አካላት ቀርቦ ተገቢውን ፍትህ የማግኘት መብት አለው:: ይህም በገንዘብ ወይም በሌላ ሊተመን የሚችል ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት መብትን ይጨምራል::

ክፍል ፫

 

 1. ማንኛውም ሰው፣ በተናጠልም ይሁን በጋራ፣ የአየር ንብረትን ከጐጂ ልቀቶች የመከላከል ግዴታ አለበት::
 2. ሁሉም ሃገራት የሰዎችን ጤናማ አካባቢ እና የተረጋጋ የአየር ንብረት የማግኘት መብት ማክበር እና ማረጋገጥ አለባቸው፣ እንዲሁም በዚህ ድንጋጌ ከክፍል ፩ እስከ ክፍል ፫ የተካተቱ መብቶችን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል:: ስለሆነም በዚህ ድንጋጌ የተካተቱ መብቶችን በተገቢ ሁኔታ ለመተግበር አስፈላጊ የሆኑ አስተዳደራዊ፣ ህጋዊ እና ሌሎች እርምጃወችን መውሰድ አለባቸው::
 3. ሁሉም ሃገራት በዚህ ድንጋጌ የተካተቱ መብቶችን እና ግዴታዎችን ማክበር አለባቸው:: ሁሉም ሃገራት በዚህ ድንጋጌ ከክፍል ፩ እስከ ክፍል ፫ የተካተቱ መብቶችን ለማክበር የሚያስችሉ ዓለማቀፋዊ ትብብሮችን ከሌሎች ሃገሮች፣ ዓለማቀፍ ድርጅቶች እና ተቌማት ጋር መፍጠር አለባቸው::
 4. ሁሉም ዓለማቀፍ ድርጅቶች እና ተቌማት በዚህ ድንጋጌ የተካተቱ መብቶችን እና ግዴታዎችን ማክበር አለባቸው::

<!– GNHRE acknowledges the important contributions of  Enyew Endalew Lijalem (Research Fellow, K.G. Jebsen Centre for the Law of the Sea, UiT Arctic University of Norway) as translator of the draft Declaration –>

ይህን ረቂቅ ድንጋጌ ወደ አማርኛ ለተረጎመልን በኖርወይ የአርክቲክ ዩኒቨርሲቲ፣ የኬ.ጅ. ጅብሰን የባህር ህግ ማዕከል፣ የፒ.ኤች.ዲ ፌለው ለሆነው ለእንዳለው ልጃለም እንዬው፥ የአለማቀፍ የሰባዊ መብት እና የአካባቢ ጥበቃ ጥምረት (ኔትወርክ) ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል::